
የሚከተለውን ክፍል ያንብቡ ወይም ያዳምጡ
10:25እነሆም አንድ ቀን፣ አንድ ሕግ ዐዋቂ ኢየሱስን ሊፈትነው ተነሥቶ፣ “መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ላድርግ?” አለው።
26ኢየሱስም፣ “በሕግ የተጻፈው ምንድን ነው? እንዴትስ ታነበዋለህ?” ሲል መለሰለት።
27ሰውየውም መልሶ፣ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህና በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ ይላል” አለው።
28ኢየሱስም፣ “በትክክል መልሰሃል፤ አንተም እንደዚሁ አድርግ፤ በሕይወት ትኖራለህ” አለው።
29ሰውየውም ራሱን ጻድቅ ለማድረግ ፈልጎ፣ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” አለው።
30ኢየሱስም እንዲህ ሲል መልስ ሰጠው፤ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ በወንበዴዎች እጅ ወደቀ፤ ልብሱንም ገፈው ደበደቡት፤ በሞት አፋፍ ላይ ጥለውት ሄዱ። 31አንድ ካህን በአጋጣሚ በዚያው መንገድ ቍልቍል ሲወርድ አየውና ገለል ብሎ አለፈ። 32ደግሞም አንድ ሌዋዊ እዚያ ቦታ ሲደርስ አየውና እርሱም ገለል ብሎ አለፈ። 33አንድ ሳምራዊ ግን እግረ መንገዱን ሲሄድ ሰውየው ወዳለበት ቦታ ደረሰ፤ ባየውም ጊዜ ዐዘነለት፤ 34ቀርቦም ቊስሎቹ ላይ ዘይትና የወይን ጠጅ አፍስሶ አሰረለት፤ በራሱም አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማረፊያ ቤት ወሰደው፤ በዚያም ተንከባከበው። 35በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለማረፊያ ቤቱ ባለቤት ሰጠና፣ ‘ይህን ሰው ዐደራ አስታመው፤ ከዚህ በላይ የምታወጣውንም ወጪ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ’ አለው።
36 “እንግዲህ፣ ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው የትኛው ይመስልሃል?”
37ሕግ ዐዋቂውም፣ “የራራለት ነዋ” አለ።
ኢየሱስም፣ “አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” አለው።
15:11ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። 12ከእነርሱም ታናሹ ልጅ አባቱን፣ ‘አባቴ ሆይ፤ ከሀብትህ ድርሻዬን ስጠኝ’ አለው፤ አባትየውም ሀብቱን ለልጆቹ አካፈላቸው።
13 “ብዙም ቀን ሳይቈይ፣ ታናሹ ልጅ ድርሻውን ሁሉ ጠቅልሎ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ በዚያም በማጋጣነት ንብረቱን አባከነ። 14እርሱም ያለውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ፣ በዚያ አገር ሁሉ ጽኑ ራብ ሆነ፤ ይቸገርም ጀመር። 15ስለዚህ ከዚያ አገር ነዋሪዎች አንዱን ተጠጋ፤ ሰውየውም ዐሣማ እንዲቀልብለት ወደ ዕርሻው ላከው። 16ዐሣማዎቹ የሚመገቡትን ዐሠር እንኳ ለመብላት ይመኝ ነበር፤ ነገር ግን ይህን እንኳ የሚሰጠው ሰው አልነበረም።
17 “ልብ በገዛ ጊዜ ግን እንዲህ አለ፤ ‘ስንቱ የአባቴ ሠራተኛ ምግብ ተርፎታል፤ እኔ ግን እዚህ በራብ ልሞት ተቃርቤአለሁ 18ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና፣ እንዲህ ልበለው፤ “አባቴ ሆይ፤ በሰማይና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ 19ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም፤ ከተቀጠሩት አገልጋዮችህ እንደ አንዱ ቍጠረኝ።’ 20ስለዚህም ተነሥቶ ወደ አባቱ ሄደ።
“ነገር ግን፣ እርሱ ገና ሩቅ ሳለ፣ አባቱ አይቶት ራራለት፤ ወደ እርሱም እየሮጠ ሄዶ ዐቅፎ ሳመው።
21 “ልጁም፣ ‘አባቴ ሆይ፤ በሰማይና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም’ አለው።
22 “አባቱ ግን አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘ፈጥናችሁ ከሁሉ ምርጥ የሆነውን ልብስ አምጡና አልብሱት፤ ለጣቱቀለበት፣ ለእግሩም ጫማ አድርጉለት፤ 23የሰባውንም ፍሪዳ አምጡና ዕረዱ፤ እንብላ፤ እንደሰት፤ 24ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፤ አሁን ግን ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር፤ ተገኝቶአል።” ከዚያም ይደሰቱ ጀመር።
25 “በዚህ ጊዜ ታላቁ ልጅ በዕርሻ ቦታ ነበረ፤ ከዚያም ተመልሶ ወደ ቤት በተቃረበ ጊዜ፣ የሙዚቃና የጭፈራ ድምፅ ሰማ፤ 26እርሱም ከአገልጋዮቹ አንዱን ጠርቶ ነገሩ ምን እንደሆነ ጠየቀው። 27አገልጋዩም፣ ‘ወንድምህ መጥቶአል፤ በሰላም በጤና ስለ መጣም አባትህ የሰባውን ፍሪዳ ዐርዶለታል’ አለው።
28 “ታላቅ ወንድሙም ተቈጣ፤ ወደ ቤትም መግባት አልፈለገም፤ አባቱም ወደ ውጭ ወጥቶ እንዲገባ ለመነው። 29እርሱ ግን መልሶ አባቱን እንዲህ አለው፤ ‘እነሆ፤ ይህን ያህል ዘመን እንደ ባሪያ አገልግዬሃለሁ፤ ከትእዛዝህም አንዱን እንኳ አላጓደልሁም፤ አንተ ግን ከባልንጀሮቼ ጋር እንድደሰት አንዲት የፍየል ግልገል እንኳ አልሰጠኸኝም፤ 30ነገር ግን ይህ ልጅህ ንብረትህን ከጋለሞቶች ጋር አውድሞ ሲመጣ፣ የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት።’
31 “አባቱም እንዲህ አለው፤ ‘ልጄ ሆይ፤ አንተ ሁል ጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤ 32ይህ ወንድምህ ግን ሞቶ ነበር፤ ሕያው ሆነ፤ ጠፍቶ ነበር ተገኘ፤ ስለዚህ ደስ ሊለንና ፍሥሐ ልናደርግ ይገ ባናል።” ’
ታሪኩን በራስዎ ቃል ለመድገም ጥቂት ጊዜ ይውሰዱ። ጮክ ብለህ መናገር ወይም መጻፍ ትፈልግ ይሆናል። ለማስታወስ እየታገልክ ከሆነ እንደገና አንብብ ወይም አድምጠው።
ታሪኩን በደንብ እንደምታውቀው ሲሰማህ ለማሰብ ጊዜ ውሰድ ወይም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ
Get Discovery Bible Studies on your phone
Discover copyright ©2015-2026 discoverapp.org
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም የቅጂ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.® ፍቃድ የተሰጠው በ Biblica, Inc.®። መብቱ በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version (Addisu Medebegna Tirgum) Copyright © 2001 by Biblica, Inc.® Used by permission of Biblica, Inc.® All rights reserved worldwide.