አግኝ

ጥናት 26

መቤዠት:ኢየሱስ ታልፎ ተሰጠ ተፈረደበትም

ዮሐንስ 18:1-40, 19:1-16

ደረጃ 1: ታሪኩን አንብብ

የሚከተለውን ክፍል ያንብቡ ወይም ያዳምጡ

x1.0

18:1ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻገረ፤ ማዶ ወደ ነበረውም የአትክልት ስፍራ ገቡ።

2ብዙውን ጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚያ ስለሚገናኝ፣ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ቦታውን ያውቅ ነበር። 3ይሁዳም ወታደሮችን እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩ ሎሌዎችን እየመራ ወደ አትክልቱ ስፍራ መጣ፤ እነርሱም ችቦ፣ ፋኖስና የጦር መሣሪያ ይዘው ነበር።

4ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወጣና፣ “የምትፈልጉት ማንን ነው?” አላቸው።

5እነርሱም፣ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት።

ኢየሱስም፣ “እርሱ እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። 6ኢየሱስም፣ “እርሱ እኔ ነኝ” ባለ ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው መሬት ላይ ወደቁ።

7እንደ ገናም፣ “የምትፈልጉት ማንን ነው?” ሲል ጠየቃቸው።

እነርሱም፣ “የናዝሬቱን ኢየሱስን” አሉት።

8ኢየሱስም መልሶ፣ “ ‘እርሱ እኔ ነኝ’ ብያችኋለሁ እኮ፤ እኔን የምትፈልጉ ከሆነ፣ እነዚህ ፣ ይሂዱ ተዉአቸው” አለ፤ 9ይህ የሆነው፣ “ከሰጠኸኝ ከእነዚህ አንድም አልጠፋብኝም” ብሎ የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው።

10ሰይፍ ይዞ የነበረው ስምዖን ጴጥሮስም፣ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ቀኝ ጆሮ ቈረጠ፤ የአገልጋዩም ስም ማልኮስ ይባል ነበር።

11ኢየሱስም ጴጥሮስን፣ “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ! አብ የሰጠኝን ጽዋ አልጠጣምን?” አለው።

12ወታደሮቹም ከአዛዣቸውና ከአይሁድ ሎሌዎች ጋር በመሆን ኢየሱስን ያዙት፤ አስረውም፣ 13በመጀመሪያ፣ የቀያፋ አማት ወደ ነበረው ወደ ሐና አመጡት፤ ቀያፋም የዓመቱ ሊቀ ካህናት ነበር። 14ቀያፋም፣ ‘ለሕዝቡ ሲባል አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል’ ብሎ አይሁድን የመከረ ነበር።

15ስምዖን ጴጥሮስና አንድ ሌላ ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉት። ይህም ደቀ መዝሙር በሊቀ ካህናቱ ይታወቅ ስለ ነበር፣ ከኢየሱስ ጋር ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ገባ፤ 16ጴጥሮስ ግን ከበሩ ውጭ ቀረ። በሊቀ ካህናቱ የታወቀው ሌላው ደቀ መዝሙርም ተመለሰና በር ጠባቂዋን አነጋግሮ ጴጥሮስን ይዞት ገባ።

17በር ጠባቂዋም ጴጥሮስን፣ “አንተ ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አለችው።

እርሱም፣ “አይደለሁም” አለ።

18ብርድ ስለ ነበር አገልጋዮቹና ሎሌዎቹ ባያያዙት የከሰል ፍም ዙሪያ ለመሞቅ ቆመው ሳሉ፣ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር።

19በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው።

20ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “እኔ ለዓለም በግልጽ ተናግሬአለሁ፤ አይሁድ በተሰበሰቡበት ምኵራብ፣ በቤተ መቅደስም ሁል ጊዜ አስተምሬአለሁ፤ በስውር የተናገርሁት የለም። 21ለምን እኔን ትጠይቀኛለህ? የሰሙኝን ጠይቃቸው፤ እነሆ፤ የተናገርሁትን እነርሱ ያውቃሉ።”

22ኢየሱስ ይህን በተናገረ ጊዜ፣ አጠገቡ ቆመው ከነበሩት ሎሌዎች አንዱ፣ “ለሊቀ ካህናቱ የምትመልሰው እንዲህ ነውን?” ብሎ በጥፊ መታው።

23ኢየሱስም፣ “ክፉ ተናግሬ ከሆነ ክፉ መናገሬን መስክር፤ እውነት ከተናገርሁ ግን ለምን ትመታኛለህ?” አለው። 24ሐናም ኢየሱስ ታስሮ እንዳለ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ላከው።

25ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ሲሞቅ፣ “አንተ ከእርሱ ደቀ መዛሙርት አንዱ አይደለህምን?” አሉት።

እርሱም፣ “አይደለሁም” ሲል ካደ።

26ከሊቀ ካህናቱ አገልጋዮች አንዱ ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ሰው ዘመድ፣ “በአትክልቱ ስፍራ አንተን ከእርሱ ጋር አላየሁህም?” ሲል ጠየቀው። 27ጴጥሮስም እንደ ገና ካደ፤ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።

28አይሁድም ኢየሱስን ከቀያፋ ወደ ሮማዊው ገዥ ግቢ ይዘውት ሄዱ፤ ጊዜውም ማለዳ ነበር። አይሁድም ፋሲካን መብላት እንዲችሉ፣ ላለመርከስ ወደ ገዥው ግቢ አልገቡም። 29ስለዚህ ጲላጦስ ወደ እነርሱ ወጥቶ፣ “በዚህ ሰው ላይ የምታቀርቡት ክስ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃቸው።

30እነርሱም፣ “ይህ ሰው ወንጀለኛ ባይሆን ኖሮ፣ አንተ ፊት ባላቀረብነውም ነበር” ብለው መለሱለት።

31ጲላጦስም፣ “እናንተ ራሳችሁ ወስዳችሁ በሕጋችሁ መሠረት ፍረዱበት” አላቸው።

አይሁድም፣ “እኛማ በማንም ላይ የሞት ፍርድ ለመፍረድ መብት የለንም” አሉት። 32ይህ የሆነው በምን ዐይነት ሞት እንደሚሞት ለማመልከት ሲል ኢየሱስ የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው።

33ጲላጦስም ወደ ግቢው ተመልሶ ኢየሱስን አስጠራና፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው።

34ኢየሱስም፣ “ይህ ሐሳብ የራስህ ነው? ወይስ ሌሎች ስለ እኔ የነገሩህ?” ሲል መለሰለት።

35ጲላጦስም መልሶ፣ “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወደ እኔ የላኩህ የራስህ ወገኖችና የካህናት አለቆች ናቸው፤ ለመሆኑ ምን አድርገህ ነው?” አለው።

36ኢየሱስም፣ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም፤ ቢሆንማ ኖሮ አይሁድ እንዳይዙኝ ሎሌዎቼ በተከላከሉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም” አለው።

37ጲላጦስም፣ “ታዲያ፣ ንጉሥ ነህ ማለት ነዋ!” አለው።

ኢየሱስም፣ “እኔ ንጉሥ እንደሆንሁ መናገርህ ትክክል ነው፤ የተወለድሁት፣ ወደዚህም ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት ለመመስከር ነው፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ይሰማኛል” አለው።

38ጲላጦስም፣ “እውነት ምንድን ነው?” አለው፤ ይህን ከተናገረ በኋላም እንደ ገና ወደ አይሁድ ወጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ የሚያስከስስ በደል አላገኘሁበትም፤ 39ነገር ግን በፋሲካ አንድ እስረኛ እንድፈታላችሁ ልማድ አላችሁ፤ ስለዚህ፣ ‘የአይሁድን ንጉሥ’ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?”

40እነርሱም እንደ ገና በመጮኽ፣ “የለም፤ እርሱን አይደለም! በርባንን ፍታልን!” አሉ። በርባን ግን ወንበዴ ነበረ።

19:1ጲላጦስም ኢየሱስን ወስዶ አስገረፈው። 2ወታደሮችም የእሾህ አክሊል ጐንጒነው በራሱ ላይ አደረጉ፤ ሐምራዊ ልብስም አለበሱት፤ 3እየተመላለሱም፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን” አያሉ በጥፊ ይመቱት ነበር።

4ጲላጦስም እንደ ገና ወደ ውጭ ወጥቶ፣ “እንግዲህ ወደ እናንተ ያወጣሁት ለክስ የሚያደርስ ወንጀል እንዳላገኘሁበት እንድታውቁ ነው” አላቸው። 5ኢየሱስ የእሾህ አክሊል ደፍቶ ሐምራዊ ልብስም ለብሶ ወጣ፤ ጲላጦስም፣ “እነሆ፤ ሰውየው!” አላቸው።

6የካህናት አለቆችና ሎሌዎቻቸውም ባዩት ጊዜ፣ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ።

ጲላጦስ ግን፣ “እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት፤ በእኔ በኩል ለክስ የሚያደርስ ወንጀል አላገኘሁበትም” አላቸው።

7አይሁድም፣ “እኛ ሕግ አለን፤ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ስላደረገ በሕጋችን መሠረት መሞት አለበት” አሉ።

8ጲላጦስ ይህን ሲሰማ የባሰውኑ ፈራ፤ 9ወደ ግቢው ተመልሶ ኢየሱስን፣ “ከየት ነው የመጣኸው?” በማለት ጠየቀው፤ ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም። 10ጲላጦስም፣ “አታናግረኝምን? ልፈታህ ወይም ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅም?” አለው።

11ኢየሱስም፣ “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ሥልጣን ባልኖረህ ነበር፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው የባሰ ኀጢአት አለበት” አለው።

12ከዚያ በኋላ ጲላጦስ ኢየሱስን ሊፈታው ፈለገ፤ አይሁድ ግን፣ “ይህን ሰው ብትፈታው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ የቄሣር ተቃዋሚ ነው” በማለት ጩኸታቸውን ቀጠሉ።

13ጲላጦስም ይህን ሲሰማ ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፤ ‘የድንጋይ ንጣፍ’ በተባለ፣ በአራማይክ ቋንቋ ‘ገበታ’ ብለው በሚጠሩት ስፍራ፣ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀመጠ። 14ቀኑ የፋሲካ በዓል መዘጋጃ፣ ጊዜውም ከቀኑ ስድስት ሰዓት ያህል ነበር።

ጲላጦስም አይሁድን፣ “እነሆ፤ ንጉሣችሁ” አላቸው።

15እነርሱ ግን፣ “አስወግደው! አስወግደው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ።

ጲላጦስም፣ “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” አለ።

የካህናት አለቆችም፣ “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለው መለሱለት።

16በመጨረሻም ጲላጦስ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው።

ወታደሮቹም ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት፤

ደረጃ 2፡ ታሪኩን እንደገና ይናገሩ

ታሪኩን በራስዎ ቃል ለመድገም ጥቂት ጊዜ ይውሰዱ። ጮክ ብለህ መናገር ወይም መጻፍ ትፈልግ ይሆናል። ለማስታወስ እየታገልክ ከሆነ እንደገና አንብብ ወይም አድምጠው።

ደረጃ 3፡ ታሪኩን አግኝ

ታሪኩን በደንብ እንደምታውቀው ሲሰማህ ለማሰብ ጊዜ ውሰድ ወይም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ


Get it on Google Play
Download on the App Store

Get Discovery Bible Studies on your phone

Discover copyright ©2015-2026 discoverapp.org

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም የቅጂ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.® ፍቃድ የተሰጠው በ Biblica, Inc.®። መብቱ በሕግ የተጠበቀ።

Holy Bible, New Amharic Standard Version (Addisu Medebegna Tirgum) Copyright © 2001 by Biblica, Inc.® Used by permission of Biblica, Inc.® All rights reserved worldwide.