አግኝ

ጥናት 4

የሰው ልጅ ውድቀት: የኖህ የጥፋት ውኃ

ዘፍጥረት 6:1-9:17

ደረጃ 1: ታሪኩን አንብብ

የሚከተለውን ክፍል ያንብቡ ወይም ያዳምጡ

x1.0

6:1ሰዎች በምድር ላይ እየበዙ ሲሄዱ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው። 2የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች የሰዎችን ሴቶች ልጆች ውብ ሆነው አዩአቸው፤ ከመካከላቸውም የመረጧቸውን አገቡ። 3 (ያህዌ)፣ “ሰው ሟች ከእርሱ ጋር ለዘላለም አይኖርም፤ ዕድሜው 120 ዓመት ይሆናል” አለ።

4የእግዚአብሔር ልጆች የሰዎችን ሴቶች ልጆች ተገናኝተው ልጆች በወለዱ ጊዜም ሆነ ከዚያም በኋላ ኔፊሊም የተባሉ ሰዎች በምድር ላይ ነበሩ። እነርሱም በጥንቱ ዘመን በጀግንነታቸው ከፍ ያለ ዝና ያተረፉ ናቸው።

5 አምላክ የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ። 6 ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ ልቡም እጅግ አዘነ። 7ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “የፈጠርሁትን የሰው ዘር ከምድረ ገጽ አጠፋለሁ፤ ከሰው እስከ እንስሳ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጡራን እስከ ሰማይ ወፎች አጠፋለሁ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቻለሁና” አለ። 8ኖኅ ግን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ሞገስን አገኘ።

9የኖኅ ታሪክ እንደሚከተለው ነው፤ ኖኅ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ጻድቅና ከበደል የራቀ ሰው ነበር፤ አካሄዱንም (ኤሎሂም) ጋር አደረገ።

10ኖኅም ሴም፣ ካምና ያፌት የሚባሉ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት።

11ምድር በእግዚአብሔር ፊት በክፉ ሥራ ረከሰች፤ በዐመፅም ተሞላች። 12እግዚአብሔር ምድር ምን ያህል በክፉ ሥራ እንደ ረከሰች አየ፤ እነሆ፤ ሰው ሁሉ አካሄዱን አበላሽቶ ነበርና 13ስለዚህ እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፦ “ሰውን ሁሉ ላጠፋ ነው፤ ምድር በሰው ዐመፅ ስለ ተሞላች በእርግጥ ሰውንም ምድርንም አጠፋለሁ። 14አንተ ግን በጎፈር ከጐኗ በር አውጣላት፤ ባለ ሦስት ፎቅ አድርገህ ሥራት። 17እኔም ከሰማይ በታች የሕይወት እስትንፋስ ያለባቸውን ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ለማጥፋት እነሆ፤ በምድር ላይ የጥፋት ውሃ አወርዳለሁ፤ በምድር ላይ ያለ ሁሉ ይጠፋል። 18ካንተ ጋር ግን ቃል ኪዳን እመሠርታለሁ። አንተና ወንዶች ልጆችህ፣ ሚስትህና የልጆችህ ሚስቶች ከአንተ ጋር ወደ መርከቧ ትገባላችሁ። 19ከአንተ ጋር በሕይወት እንዲቈዩ ከሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ተባዕትና እንስት እያደረግህ ሁለት ሁለቱን ወደ መርከቧ ታስገባለህ። 20ከእያንዳንዱ የወፍ ወገን፣ ከእያንዳንዱ የእንስሳ ወገን፣ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረት ሁሉ በየወገናቸው በሕይወት ይቈዩ ዘንድ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ አንተ ይመጣሉ። 21ለአንተና ለእነርሱ የሚያስፈልገውን ምግብ ሁሉ አከማች።”

22ኖኅም ሁሉን እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ።

7:1 (ያህዌ) ኖኅን እንዲህ አለው፤ “በዚህ ትውልድ መካከል አንተን ጻድቅ ሆነህ አግኝቼሃለሁና ቤተ ሰብህን በሙሉ ይዘህ ወደ መርከቧ ግባ። 2ከንጹሕ እንስሳት ሁሉ ሰባት ሰባት ተባዕትና እንስት፣ 3 ንጹህ ካልሆኑት እንስሳት ደግሞ ሁለት ሁለት ተባዕትና እንስት 3እንዲሁም ከወፎች ወገን ሁሉ ሰባት ተባዕትና ሰባት እንስት፣ በምድር ላይ ለዘር እንዲተርፉ ከአንተ ጋር ታስገባለህ። 4ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁ፤ የፈጠርሁትንም ሕያው ፍጡር ሁሉ ከምድር ገጽ አጠፋለሁ።”

5ኖኅም (ያህዌ) ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።

6የጥፋት ውሃ በምድር ላይ በወረደ ጊዜ ኖኅ የ600 ዓመት ሰው ነበር። 7ኖኅና ወንዶች ልጆቹ፣ ሚስቱና የልጆቹ ሚስቶች ከጥፋት ውሃ ለመትረፍ ወደ መርከቧ ገቡ። 8ንጹሕ ከሆኑትና ንጹሕ ካልሆኑት እንስሳት፣ ከወፎችና በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጡራን ሁሉ ጥንድ ጥንድ፣ 9ተባዕትና እንስት ሆነው ወደ ኖኅ መጡ፤ እግዚአብሔር ኖኅን ባዘዘውም መሠረት ወደ መርከቧ ገቡ። 10ከሰባት ቀንም በኋላ የጥፋት ውሃ በምድር ላይ መጣ።

11ኖኅ በተወለደ በ600ኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥራ ሰባተኛው ቀን፣ በዚያ ቀን የታላቁ ጥልቅ ምንጮች በሙሉ ተነደሉ፤ የሰማይ መስኮቶችም ተከፈቱ፤ 12አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ ዘነበ።

13በዚያኑ ዕለት ኖኅና ልጆቹ ሴም፣ ካምና ያፌት፣ እንዲሁም ሚስቱና ሦስቱ የልጆቹ ሚስቶች ወደ መርከቧ ገቡ። 14ከዱር እንስሳት ከየወገኑ፣ ከቤት እንስሳት ከየወገኑ፣ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጡራን ከየወገናቸው፣ ከወፎችም ከየወገናቸውና ክንፍ ያላቸው ሁሉ አብረዋቸው ገቡ። 15የሕይወት እስትንፋስ ያለባቸው ፍጡራን በሙሉ ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ወደ ኖኅ በመምጣት መርከቧ ውስጥ ገቡ። 16ከሕያዋንም ፍጡራን ሁሉ እግዚአብሔር ኖኅን ባዘዘው መሠረት ተባዕትና እንስት እየሆኑ ገቡ፤ ከዚያም (ያህዌ) ከውጭ ዘጋበት።

17የጥፋት ውሃም ለአርባ ቀናት ያለ ማቋረጥ በምድር ላይ ዘነበ፤ ውሃው እየጨመረ በሄደ መጠን መርከቧን ከምድር ወደ ላይ አነሣት። 18ውሃው በምድር ላይ በጣም እየ ጨመረና ከፍ እያለ ሲሄድ፣ መርከቧ በውሃው ላይ ተንሳፈፈች። 19ውሃው በጣም ከፍ በማለቱ፣ ከሰማይ በታች ያሉትን ታላላቅ ተራሮች ሁሉ ሸፈናቸው። 20ውሃው ከተራሮቹ ጫፍ በላይ 7 ሜትር ያህል ከፍ አለ። 21በምድር ላይ የነበሩ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ፦ ወፎች፣ የቤት እንሰሳት፣ የዱር እንስሳት በምድር የሚርመሰመሱ ፍጡራን፣ ሰዎችም በሙሉ ጠፉ። 22በአፍንጫቸው የሕይወት እስትንፋስ ያላቸው በየብስ የነበሩ ፍጡራን ሁሉ ሞቱ። 23ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ሁሉ ከምድር ገጽ ጠፉ፤ ሰዎችና እንስሳት በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራንና የሰማይ ወፎች ከምድር ላይ ጠፉ፤ ኖኅና ከእርሱ ጋር በመርከቧ ውስጥ የነበሩት ብቻ ተረፉ።

24ውሃውም ምድርን ሸፍኖ መቶ አምሳ ቀን ቈየ።

8:1እግዚአብሔር ኖኅንና በመርከቧ ውስጥ ከእርሱ ጋር የነበሩትን የዱርና የቤት እንስሳት ሁሉ አሰበ፤ በምድር ላይ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ ውሃውም ጐደለ። 2የጥልቁ ምንጮችና የሰማይ ውሃ መስኮቶች ተዘጉ፤ ዝናቡም መዝነቡን አቆመ። 3ውሃው ከምድር ላይ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጣ፤ ከመቶ አምሳ ቀን በኋላም ጐደለ። 4በሰባተኛው ወር፣ በዐሥራ ሰባተኛው ቀን መርከቧ በአራራት ተራሮች ላይ ዐረፈች። 5ውሃው እስከ ዐሥረኛው ወር ድረስ እየቀነሰ መጣ፤ በዐሥረኛው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ጫፎች ታዩ።

6ከአርባ ቀን በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቧን መስኮት ከፍቶ፣ 7ቊራን ወደ ውጭ ላከ፤ ቊራውም ውሃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር። 8ከዚያም በኋላ፣ ኖኅ ውሃው ከምድር ገጽ ጐድሎ እንደሆነ ለማወቅ ርግብን ላከ፤ 9ነገር ግን ውሃው የምድርን ገጽ ገና እንደ ሸፈነ ስለ ነበር፣ ተመልሳ ኖኅ ወዳለበት መርከብ መጣች፤ እርሱም እጁን ዘርግቶ ተቀበላት፤ ወደ መርከቢቱም አስገባት። 10ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ ኖኅ ርግቧን እንደ ገና ላካት። 11እርሷም ወደ ማታ ተመለሰች፤ እነሆም የለመለመ የወይራ ቅጠል በአፏ ይዛ ነበር፤ ያን ጊዜ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጒደሉን ዐወቀ። 12ሰባት ቀንም ቈይቶ ርግቧን እንደ ገና ላካት፤ በዚህ ጊዜ ግን ርግቧ ወደ እርሱ አልተመለሰችም።

13ኖኅ በተወለደ በ601ኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ውሃው ከምድር ላይ ደረቀ። 14ኖኅ በመርከቡ ላይ ያለውን ክዳን አንሥቶ ተመለከተ፤ የመሬቱም ገጽ እንደ ደረቀ አየ። በሁለተኛው ወር፣ በሃያ ሰባተኛው ቀን ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ደረቀች።

15ከዚያም እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፤ 16“አንተና ሚስትህ፣ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ከመርከቧ ውጡ። 17እንዲዋለዱ፣ እንዲራቡና በምድር ላይ እንዲበዙ፣ ከአንተ ጋር ያሉትን እንስሳትና በምድር ላይ የሚሳቡ ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ይዘሃቸው ውጣ።”

18ኖኅም ከልጆቹ፣ ከሚስቱና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር ወጣ። 19እንስሳቱ ሁሉ፣ ወፎችም፣ በምድር የሚንቀሳቀሱ ሁሉ በየወገናቸው ከመርከቧ ወጡ።

20ከዚያም ኖኅ መሠዊያ ሠራ፤ መሠዊያው ላይ ንጹሕ ከሆኑት እንስሳት ሁሉ፣ እንዲሁም ንጹሕ ከሆኑት ወፎች የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ፤ 21እግዚአብሔርም (ያህዌ) ደስ የሚያሰኘውን መዐዛ አሸተተ፤ በልቡም እንዲህ አለ፤ “ምንም እንኳ ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ ቢሆንም በእርሱ ምክንያት ሁለተኛ ምድርን አልረግማትም፤ አሁን እንዳደረግሁት ሕያዋን ፍጡራንን ዳግመኛ አላጠፋም።

  22“ምድር እስካለች ድረስ፣
  የዘር ወቅትና መከር፣
  ሙቀትና ቅዝቃዜ
  በጋና ክረምት፣
  ቀንና ሌሊት፣
  አይቋረጡም።”

9:1እግዚአብሔር ኖኅንና ልጆቹን እንዲህ ሲል ባረካቸው፤ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ 2አስፈሪነታችሁና አስደንጋ ጭነታችሁ፦ በዱር አራዊት፣ በሰማይ አዕዋፍ፣ በደረት በሚሳቡ ተንቀሳቃሽ ፍጡሮችና በባሕር ዓሦች ሁሉ ላይ ይሁን፤ በእጃችሁ ተሰጥተዋል። 3ሕያውና ተንቀሳቃሽ ፍጡር ሁሉ ምግብ ይሁናችሁ፤ ለምለሙን ዕፀዋት እንደ ሰጠኋችሁ፣ አሁን ደግሞ ሁሉን ሰጠኋችሁ።

4“ነገር ግን ሕይወቱ፣ ማለት ደሙ ገና በውስጡ ያለበትን ሥጋ አትብሉ። 5ሰውን የገደለ ሁሉ ስለሟቹ ደም ተጠያቂ ነው፤ የሟቹን ሰው ደም ከገዳዩ፣ ከእንስሳም ይሁን ከሰው እሻለሁ።

  6“የሰውን ደም የሚያፈስ ሁሉ፣
    ደሙ በሰው እጅ ይፈሳል፤
  በእግዚአብሔር አምሳል፣
    እግዚአብሔር ሰውን ሠርቶታልና።

7እናንተ ግን ብዙ ተባዙ፤ ዘራችሁ በምድር ላይ ይብዛ፤ ይንሠራፋ።”

8እግዚአብሔር ኖኅንና አብረውት ያሉትን ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ 9“እነሆ፤ ከእናንተና ከእናንተ በኋላ ከሚመጣው ዘራችሁ ጋር ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ 10እንዲሁም ከእናንተ ጋር ከነበሩት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ፦ ከወፎች፣ ከቤት እንሰሳት፣ ከዱር እንስሳት፣ ከእናንተ ጋር ከመርከቧ ከወጡት በምድር ላይ ካሉት ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር ኪዳን እገባለሁ። 11ከእንግዲህ ሕይወት ያለው ፍጡር ሁሉ በጥፋት ውሃ እንደማይጠፋ፣ ዳግመኛም ምድርን የሚያጠፋ ውሃ ከቶ እንደማይመጣ ከእናንተ ጋር ኪዳን እገባለሁ።”

12እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ በእኔና በእናንተ መካከል፣ ከእናንተም ጋር ካሉ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር ከሚመጣውም ትውልድ ሁሉ ጋር፣ የማደርገው የኪዳኑ ምልክት ይህ ነው፤ 13ቀስተ ደመናዬን በደመና ላይ አደርጋለሁ፤ ይህም በእኔና በምድር መካከል ለገባሁት ኪዳን ምልክት ይሆናል። 14ደመናን በምድር ላይ በጋረድሁና ቀስቴም በደመና ላይ በሚታይበት ጊዜ ሁሉ፣ 15ከእናንተና ከሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ጋር የገባሁትን ኪዳን አስባለሁ፤ ሕይወት ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ፣ ከእንግዲህ የጥፋት ውሃ ከቶ አይመጣም። 16ቀስቱ በደመና ላይ ተገልጦ በማይበት ጊዜ ሁሉ፣ በእኔና በምድር ላይ ባሉ ሕያዋን ፍጡራን መካከል ያለውን ዘላለማዊ ኪዳን አስባለሁ።”

17ስለዚህ እግዚአብሔር ኖኅን፣ “ይህ በእኔና በምድር ላይ በሚኖሩ ሕያዋን ሁሉ መካከል የገባሁት ኪዳን ምልክት ነው” አለው።

ደረጃ 2፡ ታሪኩን እንደገና ይናገሩ

ታሪኩን በራስዎ ቃል ለመድገም ጥቂት ጊዜ ይውሰዱ። ጮክ ብለህ መናገር ወይም መጻፍ ትፈልግ ይሆናል። ለማስታወስ እየታገልክ ከሆነ እንደገና አንብብ ወይም አድምጠው።

ደረጃ 3፡ ታሪኩን አግኝ

ታሪኩን በደንብ እንደምታውቀው ሲሰማህ ለማሰብ ጊዜ ውሰድ ወይም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ


Get it on Google Play
Download on the App Store

Get Discovery Bible Studies on your phone

Discover copyright ©2015-2026 discoverapp.org

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም የቅጂ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.® ፍቃድ የተሰጠው በ Biblica, Inc.®። መብቱ በሕግ የተጠበቀ።

Holy Bible, New Amharic Standard Version (Addisu Medebegna Tirgum) Copyright © 2001 by Biblica, Inc.® Used by permission of Biblica, Inc.® All rights reserved worldwide.