
የሚከተለውን ክፍል ያንብቡ ወይም ያዳምጡ
12:1 ሙሴንና አሮንን በግብፅ እንዲህ አላቸው፤ 2“ይህ ወር ለእናንተ የወር መጀመሪያ፣ የዓመቱም መጀመሪያ ይሁንላችሁ። 3ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ይህንን ንገሩ፤ ይህ ወር በገባ በአሥረኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው አንዳንድ ጠቦት ለቤተ ሰቡ፣ አንዳንድ ጠቦት ለአባቱ ቤት ያዘጋጅ። 4ማንኛውም ቤተ ሰብ ለአንድ ሙሉ ጠቦት ቍጥሩ አነስተኛ ከሆነ፣ በጐረቤት ያሉትን ሰዎች ቍጥር እስከ ቅርብ ከሆነው ጋር መካፈል ይኖርበታል፤ እያንዳንዱ ሰው በሚበላው መጠንም ምን ያህል ጠቦት እንደሚያስፈልግ መወሰን ይኖርባችኋል። 5የምትመርጡት ጠቦት በግ ወይም ፍየል ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ምንም ነውር የሌለበትና አንድ ዓመት የሞላው ተባዕት መሆን አለበት። 6ወሩ በገባ እስከ አሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቋቸው። በዚያ ምሽት ጀምበር ስትጠልቅ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ይረዷቸው። 7ከዚያም ከደሙ ወስደው የጠቦቶቹ ሥጋ የሚበላበትን የእያንዳንዱን ቤት ደጃፍ መቃንና ጉበን ይቀቡ። 8ሥጋውንም በዚያችው ሌሊት በእሳት ላይ ጠብሰው ከመራራ ቅጠልና ካልቦካ ቂጣ ጋር ይብሉት። 9ጥሬውን ሥጋ ወይም ቅቅሉን አትብሉ፤ ነገር ግን ጭንቅላቱን፣ እግሮቹንና ሆድ ዕቃውን በእሳት ላይ ጠብሳችሁ ብሉት። 10ከሥጋው ተርፎ አይደር፤ ያደረ ቢኖር ግን በእሳት ይቃጠል። 11ስትበሉም ልብሳችሁን ለብሳችሁ፣ ባጭር ታጥቃችሁ፣ ጫማችሁን አድርጋችሁ በትራችሁን ይዛችሁ በጥድፊያ ብሉት፤ (ያህዌ) ፋሲካ ነው። 12“እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ ምድር ላይ አልፋለሁ፤ ከሰውም ከእንስሳም የተወለደውን የበኵር ልጅ ሁሉ እገድላለሁ፤ የግብፅን አማልክት ሁሉ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ። 13ደሙም ያላችሁበትን ቤት ለይቶ የሚያሳይ ምልክት ይሆንላችኋል፤ እኔ ደሙን በማይበት ጊዜ እናንተን አልፋለሁ፤ ግብፅን ስቀጣ መቅሠፍቱ አይደርስባችሁም።
14“ይህን ቀን መታሰቢያ ታደርጉታላችሁ፤ በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ ቋሚ ሥርዐት ሆኖ (ያህዌ) በዓል አድርጋችሁ ታከብሩታላችሁ። 15ለሰባት ቀናት እርሾ የሌለበትን ቂጣ ብሉ፤ በመጀመሪያው ቀን እርሾን ሁሉ ከቤታችሁ አስወግዱ፤ በነዚህ ሰባት ቀናት እርሾ ያለበትን ቂጣ የበላ ማንኛውም ሰው ከእስራኤል ይወገድ። 16በመጀመሪያውና በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባዔ አድርጉ። በእነዚህ ቀናት ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩ፤ የምትሠሩት ሥራ ቢኖር ለእያንዳንዱ ምግብ ማዘጋጀት ብቻ ይሆናል።
17የቂጣን በዓል አክብሩ፤ ሰራዊታችሁን ከግብፅ ምድር ያወጣሁት በዚች ዕለት ነውና። ይህን ዕለት ለሚቀጥለው ትውልድ ቋሚ ሥርዐት በማድረግ አክብሩት። 18ከመጀመሪያው ወር ከአሥራ አራተኛው ቀን ምሽት እስከ ሃያ አንደኛው ቀን ምሽት ድረስ እርሾ የሌለበት ያልቦካ ቂጣ ትበላላችሁ። 19ለሰባት ቀን እርሾ በቤታችሁ አይኑር፤ መጻተኛም ሆነ የአገር ተወላጅ እርሾ ያለበትን ቂጣ የበላ ከእስራኤል ማኅበር ይወገድ። 20እርሾ ያለበትን ምንም ነገር አትብሉ፤ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ያልቦካ ቂጣ ነዉ መብላት ያለባችሁ።
21ከዚያም ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በሙሉ አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ቶሎ ሄዳችሁ ለየቤተ ሰቦቻችሁ የሚሆን ጠቦት መርጣችሁ የፋሲካን በግ እረዱ። 22ከዚያም ጭብጥ የሂሶጵ ቅጠል በመውሰድ፣ በሳህን ውስጥ ካለው ደም ነክራችሁ የየቤቶቻችሁን ጉበንና ግራ ቀኝ መቃኑን ቀቡ። ከእናንተ አንድም ሰው እስኪነጋ ድረስ ከቤቱ አይውጣ። 23 (ያህዌ) ግብፃውያንን ለመቅሠፍ በምድሪቱ ላይ በሚያልፍበት ጊዜ በጉበኑና በመቃኑ ላይ ያለውን ደም ሲያይ ያንን ደጃፍ አልፎ ይሄዳል፤ ቀሣፊውም ወደ ቤታችሁ ገብቶ እንዳይገድላችሁ ይከለክለዋል።
24“እናንተም ሆነ ልጆቻችሁ ይህን መመሪያ ቋሚ ሥርዐት አድርጋችሁ ትታዘዛላችሁ። 25 እሰጣችኋለሁ ብሎ በገባው ቃል መሠረት ወደ ምድሪቱ ስትገቡ ይህን ሥርዐት ጠብቁ። 26ልጆቻችሁ ስለ ሥርዐቱ ምንነት ሲጠይቋችሁ፣ 27‘ግብፃውያንን በቀሠፈ ጊዜ፣ በግብፅ ምድር የእስራኤላውያንን ቤት አልፎ በመሄድ ቤታችንን ላተረፈ፣ (ያህዌ) የፋሲካ መሥዋዕት ነው’ ብላችሁ ንገሯቸው።” ከዚያም ሕዝቡ አጐነበሱ፤ ሰገዱም። 28እስራኤላውያንም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዳዘዛቸው አደረጉ።
ታሪኩን በራስዎ ቃል ለመድገም ጥቂት ጊዜ ይውሰዱ። ጮክ ብለህ መናገር ወይም መጻፍ ትፈልግ ይሆናል። ለማስታወስ እየታገልክ ከሆነ እንደገና አንብብ ወይም አድምጠው።
ታሪኩን በደንብ እንደምታውቀው ሲሰማህ ለማሰብ ጊዜ ውሰድ ወይም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ
Get Discovery Bible Studies on your phone
Discover copyright ©2015-2026 discoverapp.org
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም የቅጂ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.® ፍቃድ የተሰጠው በ Biblica, Inc.®። መብቱ በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version (Addisu Medebegna Tirgum) Copyright © 2001 by Biblica, Inc.® Used by permission of Biblica, Inc.® All rights reserved worldwide.